በነሐሴ ወር ላይ ለጨረታ ቀርቦ ገዢ ያጣው የሜጋ አሳታሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሠራተኞቹን ጨምሮ በሥሩ ያሉ ንብረቶች በጠቅላላ ለሜጋ ማከፋፈያ እንደተላለፈ ምንጮች ገለፁ። ቢሮዎቹም ለኢፊቲን ጋዜጣ መሰጠታቸው ታውቋል።
በመስከረም ወር ላይ የጨረታ ሰነዱ ይከፈታል የተባለለትና የጨረታ መነሻው ሰባት ሚሊዮን ብር ገደማ የነበረው የሜጋ አሣታሚ ድርጅት በጨረታው መክፈቻ ዕለት በቂ ተጫራች ባለመቅረቡ ጨረታው እንደተሰረዘ ምንጮቹ ገልፀዋል።
የጨረታው መነሻ ዋጋውን ዝቅ አድርጎ በማቅረብ ተጫራቾችን በድጋሚ ለመጋበዝ ታስቦ እንደነበር የገለፁት እነዚሁ ምንጮች በመጨረሻ ይህ ሃሳብ ተቀይሮ እንዲከሰም በማድረግ ያሉት ንብረቶች እና ሰራተኞች ወደ ሜጋ ማከፋፈያ እንዲዛወሩ ተደርጓል። ከዚህ በፊት በአሣታሚ ድርጅቱ ታትመው ሲሸጡ የነበሩ መጻሕፍት በሜጋ ማከፋፈያ በኩል የሽያጭ ሥራው ይከናወናል።
በነሐሴ ወር ላይ ጨረታ የወጣባቸው ሜጋ አሣታሚ እና ሜጋ ማስታወቂያ ኢሕአዴግ «ኢንዶውመንት» ከሞላቸው ድርጅቶች መካከል ሲሆኑ ሜጋ ማስታወቂያ ባለፈው ወር ላይ ለሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ሙሉ ለሙሉ መተላለፉ ይታወሳል።