ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣው ወጪ በእጥፍ ጨመረ

በ1998 ዓ.ም የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣው ወጪ በእጥፍ የሚጨምርና ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለነዳጅ የሚወጣው ወጪ ከእጥፍ በላይ ሊጨምር የሚችለው በአሁኑ ጊዜ ያለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ እየናረ በመምጣቱና የአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ እያደገ በመምጣቱ ነው።

በመረጃው መሠረት አገሪቱ በ1996 ዓ.ም የበጀት ዓመት 1,248,092 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ውጤቶች ያስገባች ሲሆን ለዚህም ግዢ 3,08 ቢሊዮን አውጥቶ እንደነበር ይገልፃል።

በወቅቱ አንድ ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ዋጋ በአማካይ ብር 2471 እንደነበር ያስታወሰው መረጃ በ1997 ዓ.ም ደግሞ የነዳጅ ዋጋ እየናረ መጥቶ በአማካይ አንድ ሜትሪክ ቶን ከ3100 ብር በላይ በመድረሱ አገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ በማሳደግ ወደ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ እንድታወጣ አስገድዷታል።

በዘንድሮው የበጀት ዓመት ግን የነዳጅ ጭማሪው ቀደም ብለው ከነበሩ ዋጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩና የነዳጅ ፍጆታውም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እያለ በመምጣቱ አገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣው ወጪ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ተገልጿል።

ባለፉት 5 ወራትም ያለው የነዳጅ ፍጆታ ከ1997 ዓ.ም ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዋጋም ሆነ በፍጆታ መጠን ጭማሪ እያሳየ በመምጣቱ አገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣው የውጪ ምንዛሪን ሊያሳድገው መቻሉን ከድርጅቱ የወጣው መረጃ ይጠቁማል።

ባለፉት 5 ወራት የታየው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በአማካይ በሜትሪክ ቶን ከ3600 ብር በላይ ደርሷል። አገሪቱ በዚህ ዓመት ትጠቅማለች ተብሎ የሚገመተው የነዳጅ መጠንም ከ1 ሚሊዮን 350 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለነዳጅ የሚወጣው ወጪ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት አንድ ሦስተኛውን ያህል ይሆናል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በ1998 ዓ.ም በጀት የያዘው 32 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ በአገር ውስጥ አሁን እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ተገምቷል።

ከሪፖርተር ታኅሣሥ 12 ቀን 1998

ሰለ እዚህ ዜና ዋርካ ስር በአማርኛ ይወያዩ !